Tuesday, 8 July 2014

ሞትን የናቀና እስራትን ያልፈራ ትውልድ ተራራዉን ይንዳል!


“የቆጡን ላውርድ ብላ የብብቷን ጣለች::” ይላሉ ዐበው ሲተርቱ። ይህች ምስኪን ስግብግብ ፍጡር ሌላውን ስታሳድድ የያዘችው ሁሉ ይበተንባታል:: ሰሞኑ በሀበሾቹ መንደር ስጋቱ አይሏል፤ ግርግሩም በርትቷል:: እንደ ማባበልም፣ እንደ ማስጠንቀቅም፣ እንደ መቆጣትም፥ ብቻ ነገሩን በያይነቱ እየሞካከሩት ነው። እንዳለመታደል ሆኖ ለዚህ ሁሉ ችግራቸውና ስጋታቸው ምንጩ የኦሮሞ ህዝብ ብሔራዊ ትግል እንደሆነ ሊያስረዱን ይሞክራሉ። በመሠረቱ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ዓላማና ግቡ ጨቋኝ ቅኝ ገዥዎችን ማስወገድና በአንጻሩ የኦሮሞ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ለማረጋገጥ የሚካሄድ ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌዎች መሠረት ያለው ፍትኃዊ ትግል ነው። የዚህ ትግል ጠቀሜታ ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የቅኝ ገዥዎች ቀንበር በኃይል ለተጫነባቸው ለመላው የኢምፓየሪቷ ብሔሮችና ህዝቦች ጭምር ነው። በመሆኑም የኦሮሞ ሕዝብ በጭቁን ሕዝቦች የጋራ ትግል ያምናል። መሰል ዓላማና ግብ ካላቸው ኃይሎች ጋር የተቀናጀ የጋራ ትግል ያካሄዳል፤ በማካሄድ ላይም ነው። በሌላ መልኩ የኦሮሞ ህዝብ በሁለንተናዊ ባሕሪውም ሆነ በባሕላዊ አደረጃጀቱና አስተዳዳራዊ መዋቅሩ ሠላምን ይሰብካል፤ ፍትሓዊ አንድነትን ያበረታታል። ደካማውን ያፀናል፤ የተገፋውን ያቋቁማል። ለዚህ ማሳያ ደግሞ በዛሬዋ ኦሮሚያ ውስጥ ለዘመናት የኖሩ ብሔሮችና ሕዝቦች በፀረ-ኦሮሞ ኃይሎች የሚደረገውን እኩይ የማጋጨት ሤራ በማክሸፍ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ያላቸውን ተምሳሌታዊ አንድነት እንዴት ጠብቀው እንዳቆዩ ልብ ማለት ያሻል።
በአጠቃላይ የኦሮሞ ሕዝብ በማሕበራዊ አኗኗርም ሆነ በብሔራዊ ትግሉ የሰብኣዊ መብቶችን ቀመር በወጉ የተከተለ በመሆኑ በማንኛውም መመዘኛ ለጎረቤት ሕዝቦችም ሆነ አብረውት ለሚኖሩ ወንድም ሕዝቦች ስጋት ባለመሆኑ የነፍጠኛ ሥርዓት ናፋቂ ኃይሎችና አብዮታዊ ህወሃቶች (TPLF) የኦሮሞ ሕዝብን በአጠቃላይ፥ ብሔራዊ ትግሉን ደግሞ በተለይ ለማጥላላት በጋራና በተናጠል የሚያራግቡትን መሰረተ-ቢስ ወሬና የሚያደርጉትን ከንቱ ሙከራ በቀላሉ ፉርሽ ያደርጋል።
ይህ እውነታ በተለያዩ ጊዜ በተለያዩ ሰዎች ሲገለፅ ቆይቷል። ሆኖም ግን ይህንን መረዳት የተሳናቸው ኦሮሞ-ፎቢክ የሆኑ (Oromo-phobia) ፍርሃተ-ኦሮሞ የተጠናወታቸዉ ኃይሎች ተገደውም ብሆን እጃቸውን እስኪሰጡ ድረስ የኦሮሞ ትግል እምርታ በቃልም ሆነ በተግባር ልናሳያቸውና ልናስተምራቸው ግድ ይለናል። በዚሁ መሠረት የኦሮሞ ህዝብ ትግል በማንኛውም ዓይነት ሤራ መቀልበስ የማይቻል እጅግ ወሳኝ ደራጃ ላይ ስለመድረሱ ባይወዱም ምስጢን ከነተጨባጭ መስረጃዎቹ ላሳያችሁ ወደድኩ።
ማሳያ ቁጥር አንድ፥ የኦሮሞ ሕዝብ ውድ ልጆቹ በከፈሉት ክቡር ዋጋ የሀገሩን ድንበርና የህዝቡን እውነተኛ ታርክ እስከ ወዲያኛው የዓለም ጫፍ ድረስ ለማስተዋዋቅ ችሏል። ከእንግዲህ ወዲያ ሀገራችን ኦሮሚያ በልጆቿ ደምና አጥንት እስከ ዘልዓለሙ ትከበራለች! በቃ እውነታው ይህ ነው።
ማሳያ ቁጥር ሁለት፥ የኦሮሞ ህዝብ ባህልና ቋንቋ አስተማማኝ በሆነ መልኩ በማይናውጥ መሠረት ላይ ተዋቅሯል። ዛሬ Afaan Oromoo ምቹ የሆነ የራሱ ፊደል (orthography) አለው። ሚልዮኖች ይማሩታል፤ ያስተምሩበታል፤ ይመራመሩበታል። እጅግ በርካታ ዓለምዐቀፋዊ ይዘት ያላቸዉ ሚዲያዎች ይዘግቡበታል፤ ያሰራጩበታል። የስነ-ፅሁፍና ስነ-ጥበብ ውጤቶች ይቀርብበታል፤ ይከወንበታል። ይህም የኦሮሞ ህዝብ ትግል ወደ ፊጻሜው እየተቃረበ ስለመሆኑ አንዱ አመላካች መስረጃ ነውና ልብ ይሉታል።
ማሳያ ቁጥር ሦስት፦ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ሞትን በናቁ፣ ሕይዋታቸውን ጨምሮ ሙሉ ሰብኣዊ ክብራቸውን ለኦሮሚያ ሉዓላዊነትና ለኦሮሞ ነጻነት ቤዛ ሊያደርጉ የወሰኑ የአንድ ትውልድ ዘመን ላይ ደርሷል። ይኸኛው የነገሮች ሁሉ ማሳረጊያ ይሆናል። እውነታው በተግባር እየታያ ስለሆነ የማሳመኛ ትንታኔ የሚያስፈልግ አይመስለኝም።
ማሳያ ቁጥር ዐራት፦ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ዘግናኝና ወደርየለሽ ጭፍጨፋ የዓለምዓቀፉ ማሕበረሰብ በግልፅ ከመረዳትም አልፎ ለመፍትሔው ሁነኛ ምክክሮችን ለማድረግ የተገደደበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። ይህም ያልተቋረጣ ህዝባዊ ትግል ፍሬ ነውና ባይጥማሁችም ትክክለኛ ትርጉሙን የምትስቱ አይምስለኝም።
ማሳያ ቁጥር አምስት፦ ዛሬ የኦሮሞ ህዝብ በፀረ-ኦሮሞ ኃይሎች ሤራ የማይከፋፈልና ለጋራ ዓላማ ያለአንዳች ልዪነት በጋራ መቆማቸውን ያረጋገጡበት ታርካዊ ወቅት ላይ ደርሷል። ይህ የኦሮሞ ህዝብ የጋራ ትብብር የአራት ኪሎዉን አሮጌ ዙፋናችሁን ከነመሠረቱ ለመጣል መነቅነቅ በመጀመሩ የአንዳንዶቻችሁ የደም-ግፊት ልክ ስለመጨመሩ የሰሞኑ ግርግር አመላካች ሆኗል።
ማሳያ ቁጥር ስድስት፦ የኦሮሞ ህዝብ ብሔራዊ ትግል ሁለንተናዊ የትግል ስልቶችን የሚከተል እንደመሆኑ መጠን የኦሮሚያ ተራሮች፣ ሸለቆዉ፣ ጫካዉ ጋራዉና ሸንተረሩ ትግሉን ወደ ፊጻሜ የሚያደርስ መጠነ-ሰፊ የትጥቅ ትግልና ጠንካራ ወታደራዊ ዝግጅቶችን እያስተናገዳ ይገኛል። በዚሁ መሠረት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (Oromo Liberation Army) በወርሃ ግንቦት (2014ዓም) ብቻ ከድንበር እስከ መሃል ኦሮሚያ ድረስ በመንቀሳቀስ በወሰደዉ ወታደራዊ ጥቃት ከሁለት መቶ በላይ የጠላት ሠራዊትን ሙትና ቁስለኛ አድርጓል። እንዲሁም በርካታ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለመማረክ ችሏል።
በአጠቃላይ የኦሮሞ ህዝብ በትግሉ እጅግ ቁልፍ ድሎችን እያስመዘገበ ሲሆን ለቀሪ መብቶቹ ሙሉ ለሙሉ መከበር ደግሞ ሰብኣዊና ቁሳዊ ኃይሉን ከመቼም በላይ አቀናጅቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ታዲያ ህዝባዊ ዓላማ ይዞ በቆራጥነት የተነሳዉን ባለራዕይ ትዉልድ በእስራትና ግዲያ ልታቆሙት ነዉን? ወይስ በበግ መሳይ ተኩላዎች ግሳጼና የማወናባጃ ቃላት ልታዘናጉት ትሻላችሁ? እውነት! እውነት እላችኋለሁ! ያ ዘመን ዳግም ላይመለስ ሄዷል። አሁን እውነቱን ትቀበሉ ዘንድ ላደፋፍራችሁ። ግርግሩ፣ ሽኩቻው፣ የመሠሪዎች ሤራ … ብቻ ማንኛውም ዓይነት የክፋት ኃይል ይህንን ትውልድ ሊያቆመው አይችልም። ለምን ቢባል ይህ ትውልድ ዓላማ ይዞ የተነሳ፣ ለዘመናት በህዝባዊ ተልዕኮ ተቀርጾ፣ በጽናት የታነጻ፣ መነሻውንና መድረሻውን ጠንቅቆ ያወቀ፣ ሞትን ንቆ ዋጋውን ተምኖ የወጣ ትውልድ ነውና በተዓምር የሚያቆመዉ ምድራዊ ኃይል የለም፥ አይኖርምም። አሁንማ ብቸኛዉና አዋጪው መንገድ በትላንትናዉ አሮጌ መነፅራችሁ እዉነትን ኣጣምማችሁ በማየት ከመስጋት ይልቅ እይታችሁን በማስተካከል ማምለጥ የማይቻለዉን ሀቅ በመቀበል ከነባራዊ እውነታ ጋር ታርቆ መኖር ነዉ የሚሻላችሁ። ልቦና ይስጣችሁ!
እዉነት ለዘለዓለሙ ታሸንፋለች!

ጂቱ ለሚ

No comments:

Post a Comment