Saturday, 30 November 2013

እስራኤል ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 60ሺህ አፍሪካውያንን አስወጣለሁ አለች


እስራኤል ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 60ሺህ የሚጠጉ አፍሪካውያን ስደተኞችን ከሃገሯ እንደምታስወጣ ያስታወቀች ሲሆን በህገወጥ መንገድ በሊቢያ የሚኖሩ ከ120 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ወደ ሃገራቸው ይመለሳሉ ተብሏል፡፡ የእስራኤል ካቢኔ ባለፈው እሁድ ስደተኞቹን የሚያስወጣ አዲስ ህግ ካፀደቀ በኋላ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያዊን ኔትያሁ፣ ህገወጥ ስደተኞቹን ከሀገራቸው እንደሚያስወጡ አስታውቀዋል፡፡ የአገሪቱ ካቢኔ ባፀደቀው መመሪያ መሰረት እስራኤል በመጀመሪያው ዙር 4ሺ ስደተኞችን የምታስወጣ ሲሆን በቀጣይም በዘላቂነት ህገወጥ ስደተኞች ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ በዘላቂነት ለመከላከል ከግብጽ የምትዋሰንበትን ድንበር ጥበቃ እንደምታጠናክር ገልፃለች፡፡ ከሀገሪቱ ይወጣሉ ተበለው የሚጠበቁት አብዛኞቸ ሱዳናውያንና ኤርትራውያን ሲሆኑ ኢትዮጵውያኑም የገፈቱ ቀማሽ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሊቢያን ማረፊያ ያደረጉ ከ120 በላይ ኢትዮጵያውያን በግብጽ ካይሮ ባለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትብብር የጉዞ ሰነዳቸው ተዘጋጅቶላቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በአለማቀፍ የስደተኞች ተቋም (IOM) ትብብር እንደሚመለሱ ታውቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በባህሬን በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ትሠራ የነበረች ኢትዮጵያዊት በሶስት ወንዶች ተጠልፉ መደፈሯንና በሴተኛ አዳሪነት እንድትሰራ መገደዷን ገልፃ፤ ድርጊቱን ፈጽሟል የተባለውን ባንግላዲሻዊ እንደከሰሰች ሰሞኑን ተዘግቧል፡፡ የ28 አመቷ ኢትዮጵያዊት ቆሻሻ ለመድፋት ወደ ውጪ ስትወጣ ሁለት ማስክ ያጠለቁ ወንዶች አፍነው በመውሰድ አፓርታማ ቤት ውስጥ ከነበሩ አራት የተለያዩ አገራት ሴቶች ጋር በሴተኛ አዳሪነት እንድትሰራ መደረጓን ገልፃለች፡፡ በቀን አስር ጊዜ ያህል ከተለያዩ ወንዶች ጋር ወሲብ እንድትፈጽም ትገደድ እንደነበርም ለፍ/ቤት አስረድታለች፡፡

No comments:

Post a Comment