Wednesday 26 February 2014

ምነው ሚኒስትር ዘነቡ ?






ትናንት ማታ የሴቶች፣ ሕጻናትና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዘነቡ በትዊተር ገጻቸው ላይ ግብረ ሰዶምን
በተመለከተ የጻፉትን ነገር ከምመለከት ወይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባይኖር ወይ እርሳቸው ሚኒስትር ባይሆኑ
እመርጥ ነበር፡፡ የሴቶችና የወጣቶች፣ የሕጻናት ሚኒስትር ሆነው ግብረ ሰዶምን በመደገፍና የዑጋንዳን አዲሱን
ሕግ በመቃወም መጻፋቸው ‹‹ይህቺ ሀገር ወዴት እየሄደች ነው›› ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል፡፡ ከተወሰኑ ጊዜያት
በፊት በአዲስ አበባ የተሾሙ የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ የግብረ ሰዶማውያን መብት እንዲጠበቅ እሠራለሁ
ያሉትን አስታውሼ እኒህ ዲፕሎማት እውነትም ሠርተዋል ማለት ነው አልኩ፡፡
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የኤች አይ ቪ ኤድስ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሲደረግ የእምነት ተቋማት መሪዎች ግብረ
ሰዶምን በመቃወም መግለጫ ለመስጠት ተዘጋጅተው ወዲያው ነበር የተሠረዘው፡፡ ግብረ ሰዶማውያንን ተዋቸው
ተብለው መግለጫቸው መሠረዙ፣ እነርሱም ያንን በዝምታ ማለፋቸው በሀገራችን ከተከናወኑ አሳዛኝ ተግባራት
አንዱ ሆኖ እንዲመዘገብ አድርጎታል፡፡
ዑጋንዳ ሕጉን ያወጣችው የግብረ ሰዶማውያንን ተግባር ለመከታተል፣ ለመቆጣጠርና ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ
ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕግም ግብረ ሰዶም ወንጀል መሆኑን ከዑጋንዳ ቀድሞ የደነገገ ነው፡፡ ምነው ሚኒስትራችን
የግብረ ሰዶም ደጋፊ ሆነው ብቅ አሉ፡፡ ይህ ሕግኮ እርሳቸውንም የሚመለከት ነው፡፡ ግብረ ሰዶም በሀገሪቱ
በድብቅ እየተድፋፋ ሕጻናትና ወጣቶችን እየቀጠፈ፣ ማኅበረሰባዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችንን እያፈረሰ ነው፡፡
ሰውን ከተፈጠረበት ዓላማና ግብር ውጭ የሚያደርግ ነው ግብረ ሰዶም፡፡ እንስሳት እንኳን የማይፈጽሙትን
የሚያስደርግ ነው ግብረ ሰዶም፡፡
ምዕራባውያን በራሳቸው ምክንያት የተነሣ የዚህ ሐሳብ ደጋፊም አቀንቃኝም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነርሱ የደገፉትን
ሁሉ የመደገፍ ግዴታ ግን የለብንም፡፡ የእነርሱ ማኅበረሰባዊ ሥሪትና የእኛ ሥሪት ፈጽሞ አይገናኝም፡፡ በርግጥ
ይህንን መሰል ርካሽ ነገሮችን መደገፍና ማቀንቀን ዓለም ዐቀፍ ተቀባይነትን ለማግኘት አቋራጭ መንገድ መሆኑ
ይታወቃል፡፡ እኛ ግን ሚኒስትራችን የምንፈልጋቸው ለአሜሪካ ጉዳዮች አይደለም፤ ለኢትዮጵያ ጉዳዮች እንጂ፡፡
እርስዎ የተሾሙላቸው ሕጻናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ሥራ፣ ንጹሕ ውኃ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የጤና ተቋማት፣ ሰብአዊና
ፖለቲካዊ መብቶች ቸግሯቸው እንጂ ግብረ ሰዶምነት አልቸገራቸውም፡፡ ግብረ ሰዶምነት የእነርሱ ማጥቂያ
መሣሪያ እንጂ ክብርት ሚኒስትሯ የሚቀኙለትና የሚሟገቱለት አይደለም፡፡
ለሕጻናት፣ ለወጣቶችና ለሴቶች ያልተሠራ ብዙ አጀንዳ ባላት ሀገር፣ በዐቅም እጥረት በጤና ተቋማቱ የማይወልዱ
እናቶች፣ በየጉራንጉሩ የሚወለዱ ሕጻናት፣ በየጫት ቤቱ ሥራ ፈትተው የሚባዝኑ ወጣቶች ያሏት ሀገር ግብረ
ሰዶምን ጉዳዬ ብላ ማቀንቀኗ በዜጋ ላይ የሚፈጸም ስላቅ ነው የሚሆነው፡፡
እኔ ይህ መልእክት አሁንም የእርሳቸው ባይሆን እመርጣለሁ፡፡ ማብራሪያ እንደሚሰጡበትም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡


  ሚኒስትሯስ ምን ይላሉ? 
ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዘነቡ ለታድያስ አዲስ ዛሬ በ9 ሰዓት በሰጡት መግለጫ ‹‹ከልብ ነው ያዘንኩት፤ የእኔም አቋም
አይደለም፤ የመንግሥትም አቋም አይደለም፤ ያየሁትም በትናንትናው ዕለት ነው፤ በሆነውም ነገር በጣም ነው
ያዘንኩት፤ በተፈጠረው ነገር ሰብእናዬ ተጎድቷል፡፡ እስከ መጨረሻ ማጣራት ያለብኝን አጣራለሁ፡፡ ይህ በሀገሪቱ
ሕግ ላይ የተቀመጠ ወንጀል ነው፡፡ ከእኔ ሰብእናም ጋር አይሄድም›› ብለዋል፡፡ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች
ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሽመልስም ‹‹አካውንታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተጠልፏል›› ብለዋል፡፡

No comments:

Post a Comment