Thursday 6 March 2014

አሟሟታቸው “ሆድ ይፍጀው” የተባለው የኦቦ ዓለማየሁ ቀብር ቅዳሜ ይፈጸማል፤ አስቴርና ሙክታር አስከሬኑን ለማምጣት ባንኮክ ናቸው

(ዘ-ሐበሻ) በባንኮክ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ያረፉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ኦቦ ዓለማየሁ አቶምሳ የቀብር ስነ ሥርዓት የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ እንደሚፈጸም ታወቀ። አስከሬናቸውን ከባንኮክ ለማምጣትም ወ/ሮ አስቴር ማሞና አቶ ሙክታር ከድር ባንኮክ የገቡ ሲሆን ዛሬ ምሽት 3 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።



በ45 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ኦቦ ዓለማየሁ የክልሉን ፕሬዚዳንትነት ከተቀበሉ በኋላ መርዝ እንደተሰጣቸውና ለበርካታ የአልጋ ቁራኛ እንዲሆኑ አድርጓቸው፤ በህክምና ላይ የሰነበቱ ሲሆን አሟሟታቸውም ሆድ ይፍጀው ሆኗል ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች።
የአቶ ዓለማየሁ አቶምሳ የቀብር ስነ ሥርዓት የፊታችን ቅዳሜ በቅድስት ስላሴ ቤ/ክ እንደሚፈጸም የታወቀ ሲሆን አስከሬናቸውን ለማምጣትም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ሪፎርም ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት ኦቦ ሙክታር ከድር እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቀው ወ/ሮ አስቴር ማሞ ባንኮክ ተጉዘዋል። እነዚህ ሁለት ባልስልጣናትም አስከሬኑን ይዘው ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከባለስልጣኑ ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበረን ያሉ ሁለት አስተያየት ሰጪ ጋዜጠኞች በፌስቡክ ገጻቸው ከፕሬዚዳንቱ አሟማት ጀርባ ምስጢር አለ እያሉ ነው። የሁለቱንም አስተያየት ያንብቡት፦
በቅድሚያ የጋዜጠኛ ደመቀ ከበደ አስተያየት
” የ3 ልጆች አባት የነበሩትን አቶ አለማየሁ አቶምሳን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እንደተሾሙ ሰሞን ለዘገባ አጭር ቃለ መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር – አዳማ ላይ፡፡ ሰውየው በሙስናና ሙሰኞች ላይ የመረረ አቋማቸውን ሲነግሩኝ ‹‹ቆራጥነት›› ባዘለ ቃና ነበር፡፡
ይህንን በተግባርም አሳይተዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
ግን ብዙ ሳይቆዩ መታመማቸው ተሰማ፤ የህመማቸው ምክንያቱ ደግሞ የሌባ ጠላት መሆናቸው ነው ተባለ፡፡ ‹‹ድሮስ አሰለጥ ሌባ መች ለጠላቱ ይተኛል›› … በሚል ነገሩ ወዲህና ወዲያ ተነዛ፡፡ ተጨባጭና ሁነኛ መልስ ግን ያገኘ አላጋጠመኝም፡፡
እንደ ጥላሁንን ገሰሰ ሆድ ይፍጀው ሁላችንም የህመማቸው ምክንያቱን ብንጠብቅም ‹‹በየጊዜው ደም እየቀየሩ ነው ከህመማቸው የሚያገግሙት›› ከሚል ወሬ በቀር ሀቁን ይሄ ነው ያለ የለም፡፡ ከእሳቸው አንደበትም የተሰማ ነገር የለም – እስከማውቀው ድረስ፡፡
ይህ በእንጥልጥል እንዳለ ሰሞኑን ስልጣናቸውን በህመም መልቀቃቸውን ሰምተን ብዙ ሳንቆይ ዛሬ ደግሞ ‹‹ከዚህ ዓለም መለየታቸውን›› አደመጥን፡፡ አቶ ሙክታር ከድርና ወ/ሮ አስቴር ማሞ እየታከሙ ከነበረበት ‹‹ባንኮክ›› ከቤተሰባቸው ጋር ‹‹አስከሬናቸውን›› ሊያመጡ እዚያው መገኘታቸውም ተነግሯል፡፡
ያሳዝናል፡፡ በዚህ ዕድሜ መሞታቸው ብቻ ሳይሆን የአገርን ሙስና ‹‹አፈር ድሜ›› ለማብላት ቁርጠኛነትን ‹‹ለሌሎቹ ሳያሳዩልን›› ሞት ስለቀደማቸው ያሳዝናል፡፡
ከአቶ አለማየሁ አቶምሳ ያጣነው አለ – የሌባ አዳኝ መሆንን!
!”
የሰንደቅ ጋዜጣ አዘጋጅ ፍሬው አበበ በበኩሉ እንዲህ ብሏል፦
“የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት የአቶ አለማየሁ አቶምሳ ዜና ዕረፍት ስሰማ እጅግ አዝኛለሁ፡፡ አቶ አለማየሁን በአካል የማውቃቸው በ2002 ዓ.ም ወሩን በማላስታውሰው ጊዜ ለስራ የቢሮአቸውን ደጃፍ በረገጥኩበት ወቅት ነበር፡፤ ያኔ አቶ አለማየሁ የማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ ነበሩ፡፡ ለቀጠሮ በቢሮአቸው ድንገት ስገኝ ምናልባት ቢያናግሩኝ በሚል ቀቢጸ ተስፋ በመሰነቅ ነበር፡፡ በአጋጣሚ አቶ አለማየሁ በቢሮአቸው ውስጥ ነበሩና እንድገባ ፈቅደውልኝ በጨዋ ደንብ ከመቀመጫቸው ተነስተው በአክብሮት ያደረጉልኝ አቀባበል ምናለ ሌሎቹም ሹማምንት ከሳቸው ቢማሩ የሚያሰኝ ዓይነት ነበር፡፡ ተግባቢ ሰው በመሆናቸው ከሄድኩበት ርዕሰ ጉዳይ ውጪ ስለግሉ ፕሬስ ላይ ላዩን ለመነጋገር ችለናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አቶ አለማየሁ የግሉ ፕሬስ መኖርና መጠናከር ለስርኣቱ ግንባታ ወሳኝ ነው ብለው የሚያምኑ ቀና ሰው መሆናቸውን ለመረዳት ችያለሁ፡፡ በወቅቱ ፍጹም ጤነኛ እና የተረጋጉ፣ ትልቅ የመሪነት ካሪዝማ ያላቸው ሰው እንደሆኑ በአጋጣሚ መታዘብ ችዬ ነበር፡፡
እናም የክልሉ ፕሬዚደንትና የኦህዴድ ሊቀመንበር ሆነው ከተሾሙ ጥቂት ወራት ግዜ በኃላ ከባድ ሕመም ላይ መውደቃቸው በእርግጥም ከጀርባቸው የተሸረበባቸው ተንኮል (ሴራ) ስለመኖሩ በብርቱ እንድንጠረጥር በር የሚከፍት ነው፡፡ ነፍስ ይማር!!”

እውነት እየቆየ መውጣቱ አይቀርም፤ የዘ-ሐበሻ አንባቢዎችስ ምን ትላላችሁ?

No comments:

Post a Comment